የአከባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ስልጣን እና ተግባርራት
-
የአካባቢ ጥበቃ ስታንዳርድ ያዘጋጃል፤ አካባቢ እንዳይበከል የመከላከያ ስልት ይቀይሳል፣ አግባብ ያላቸውን አካላት ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ያስተባብራል፤
- የአካባቢ ጥበቃ፣ የተፈጥሮ ሀብትና የዘለቄታ አጠቃቀም እንዲኖርና እንዳይባክን ተገቢ ግንዛቤ ይፈጥራል፤ ስለ አካባቢ ጥበቃ በተለያዩ መድረኮች፣ አደረጃጀቶች እና በመገናኛ ብዙሃን ትምህርት ይሰጣል፤
- ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ልማትን ተግባራዊ እንዲሆን ያስተባብራል፤
- ከኢንዱስትሪ ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚመነጩ ዝቃጭ፣ ተረፈ ምርት፣ ቆሻሻ በሕግ መሠረት መወገዱን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ በህግ አግባብ እርምጃ ይወስዳል፤ እንዲወሰድ ያደርጋል፤
- ታዳሽና አማራጭ የኢነርጂ ምንጮች እና ቴክኖሎጂዎችን ያፈላልጋል፣ ያሻሽላል፤ ያሰርጻል፤ ያስፋፋል፤
- ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚመነጩ የአየር፣ የድምጽ እና የፍሳሽ ብክለትን በህግ መሰረት ይቆጣጠራል፤ እርምጃ ይወስዳል፤ እንዲወሰድ ያደርጋል፤
- የአካባቢ ጥበቃ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የማምረቻና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና ሌሎች አካባቢ ላይ ተፅእኖ የሚያሳድሩ አካላት የብክለት መከላከል የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፤
- የከተማው የካባና ሌሎች ተቆፋሪ ማዕድናት ሥፍራዎች ያላቸውን የማዕድን ክምችት መጠን ይለያል፤ ለልማት ያዘጋጃል፤ ከአደጋ ነጻ መሆኑን ያረጋግጣል፤
- የካባ ማምረት ሥራ ለሚያካሂዱ ፈቃድ ይሰጣል፤ ቁጥጥር ያደርጋል፤
- የተለያዩ ማዕድናት ቁፋሮ የተካሄደባቸውን ቦታዎች መልሰው የሚለሙበት የአሰራር ሥርዓት ይዘረጋል፤ ተግባራዊነቱን ያረጋግጣል፤
- የተለያዩ ዕፅዋት የሚተከሉበትን ቦታና የሚሰጡትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታ በማጥናት ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ በከተማው መዋቅራዊ ፕላን ለመናፈሻ፣ ለደን፣ ለወንዝ ዳርቻና ለሌላ አረንጓዴ ቦታ ልማት በተከለሉ ቦታዎች ላይ የሚተከሉትን ዕፅዋት አይነት በሚመለከት ያማክራል፤ ያስተዋውቃል፤
- ልተሞከሩና የማይታወቁ ከአካባቢ ጋር ተስማሚና ጠቃሚ የሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች በከተማው ማልማት ለሚፈልጉ ሰዎች ፈቃድ ይሰጣል፤
- በመንግስትም ሆነ በግል የይዞታ ክልል የለሙ ዛፎችን ለመቁረጥ ሲፈለግ ፈቃድ ይሰጣል፣ ከባለስልጣኑ ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ እንዳይቆረጡ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፤
- በአስተዳደሩ ይዞታ ስር የሚገኙ ጥብቅ የደን ቦታዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎች፣ የጋራ መገልገያ አረንጓዴ ቦታዎች ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤
- በተፋሰስና በአረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አገልግሎት ዘርፎች መሠማራት ለሚፈልጉ የግል ባለሀብቶች፣ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ ነዋሪዎች ወይም ሌሎች አካላት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፤ ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤
- ዓላማውን ከግብ ሊያደርሱ የሚችሉ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ያከናውናል፡፡